መንግሥት በፕላቲክ መልሶ መጠቀም ለተሰማሩ ኩባንያዎች ልዩ ድጋፍ አንዲሰጥ ተጠየቀ

የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሰው ጥቅም ላይ የሚያውሉ ድርጅቶች ከ 10 አይበልጡም
ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የፕላስቲክ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ለውጦች እየታዩ ቢሆንም ከብክለት ነጻ አንድትሆን ፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ መጠቀም ላይ ብዙ ሊሰራ ይገባል ሲል የአዲስ ቻምበር ጥናት አመለከተ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ያስጠናው ጥናት አንደሚጠቁመው የዛሬ 10 አመት ገደማ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ በአመት በአማካይ ወደ 6ኪሎ ፕላሲቲክ ውጤቶችን ሲጠቀም አንደነበር ሲያመለክት ይህ አኃዝ ዛሬ ላይ መጠኑ ወደ 50 ኪሎ ማደጉን አመልክቷል፡፡

ጥናት አቅራቢው አቶ አቤል ግርማ ከተማዋ ጽዱ፤ሳቢ እና ለቢዝነስ ምቹ አንድትሆን በተለይ የቆሻሻ አወጋገድ ባሕላችን ሊሻሻል ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ይሁንና ብረታብረቶችን ፤የወረቀት ውጤቶች ፤የሚበሰብሱ እና ፕላስቲክ ውጤቶችን ለይቶ የማስወገድ ልምድ በጣም አነስተኛ ነው፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ወጣቶችን እና ሴቶችን በጥቃቅን እና አነስተኛ ኤንተርፕራይዝ በማደራጀት በቆሻሻ አሰባሰብ ላይ ማሰማራቱ በመልካም የሚታይ ነው ብለዋል፡፡

በአቅርቦት አንጻር የተሰራው ሥራ የሚያበረታታ መሆኑም ተመላክቷል፡፡ ነገር ግን ከፍላጎት አንጻር ሲታይ ከከተማይቱ ከሚሰበሰበው የፕላስቲክ ቆሻሻ አንደገና መልሶ ጥቅም ላይ የሚውለው በአመት ከ65 ሺህ ቶን አይበልጥም ፡፡

በተለይ በየቀኑ ከየቦታው ያገለገሉ የፕላስቲክ ውሃ ጠርሙሶችን እየለቀሙ ለፋብሪካዎች በማቅረብ በርካቶች እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ፡፡

ነገርግን ያገለገሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን መልሰው ጥቅም ላይ የሚያውሉ ፋብሪካዎች ቁጥር ከ10 አይበልጡም፡፡

ይህ ቁጥር ከሁሉም የከተማዋ ማዕዘን የሚሰበሰበው የፕላስቲክ ቆሻሻ መጠን ጋር ሲታይ አዚህ ግባ የሚባል አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

ሌላኛው ጥናት አቅራቢ ገዛኸኝ መገርሣ በበኩላቸው እነዚህ ፋብሪካዎች መልሰው ያመረቱትን ፕላስተክ ወደ ውጪ ገበያ ልከው በአመት እስከ 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አስገኝተዋል፡፡

ስለዚህ መንግሥት ይህን አዋጪ ፤አካባቢን ከብክለት የሚከላከል እና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊደግፈው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ ቻምበር ም/ዋና ጸሐፊ አቶ ዘካርያስ አሰፋ ጥናቱን በግብአት ለማበልጸግ በተጠራው ዝግጅት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስ ቻምበር በንግድና ኢንቨስትመንት አንቅስቀሳሴ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ኩነቶችን እየተከታተለ ጥናት በማካሄድ በመረጃ የተደገፈ የፖሊሲ ማሻሻያ ግብዓት ለመንግሥት ሲያቀርብ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ጽዱ አና አረንጋዴ ለማደረግ በሚደረገው ጥረት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የንግዱን ሕብረተሰብ በማስተባበር የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *