መንግስትና ነጋዴው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተባብረው መስራት የሚገባቸው ወቅት-በሙሉጌታ ጉደታ

በሰላሙ ጊዜ መንግስትና የንግዱ ማህበረሰብ በብዙ የፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ወይም አብረው መስራት ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ የግሉን ሴክተር ችግሮች ለመፍታት በሚደረግ ትግል መንግስትና ነጋዴው በተቃራኒ አቅጣጫዎች ሲጓተቱ ቆይተዋል፡፡ ለውጡ በመጣባቸው ባለፉት ሁለት አመታት እንኳን የአመራርና የመዋቅር ለውጥ ቢታይም በመንግስት ፖሊሲ አስፈፃሚዎች አካባቢ የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ለውጥ ባለመካሄዱ የንግዱ ማህበረሰብ እምብዛም ተጠቃሚ ሲሆን አልተስተዋለም፡፡ ጥያቄዎች በይደር እንዲቆዩ አለበለዚያም ጨርሰው ችላ እንዲባሉና እንዲረሱ ተደርገው ነበር፡፡ ነጋዴው በንግድ ፖሊሲ፣ በቀረጥ አጣጣልና በፋይናንሱ ሴክተር የሚታዩት ድክመቶች እንዲታረሙ ያልጠቆጠበ ጥረት ቢያደርግም ጥያቄዎቹ መልስ ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡

አንፃራዊ ሰላም በሚሰፍንበት ጊዜ የመንግስት የገንዘብና የብድር ፖሊሲዎች ለሚፈጥሩት የዋጋ ግሽበት ወይንም የዋጋ ንረት ችግሮች የንግዱ ማህበረሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ሲሆንና ሲወቀስ ኖሯል፡፡ በንግዱ ማህበረሰብ አካባቢ አንዳንድ አጥፊዎች ቢኖሩም ነጋዴውን በጅምላ መፈረጅ የተለመደ ነገር ነበር፡፡ ነጋዴው ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ገንቢ ሃሳቦችን ቢያቀርብም ተደማጭነት አግኝቶ ነበር ማለት ግን አይቻልም፡፡ የአገራችን ኢኮኖሚ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ሲሄድ ነጋዴው የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ቢጠቁምም አድማጭ ሳያገኝ እዚህ ደርሷል፡፡

እነሆ አሁን ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የነበረውን እንዳልነበረ በማድረግ ብዙ ነገሮችን እያበላሸ ይገኛል፡፡ ወረርሺኙ በተከሰተ ሁለት ወራት ሳይሞላው ኢኮኖሚው ድቀት ውስጥ መግባቱ ለማንም ሰው ግልፅ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወረርሽኙ እየተባባሰ ከሄደ ደግሞ ምን ልፈጠር ይችላል የሚለው ጥያቄ መንግስትን ብቻ ሳይሆን የግሉን ሴክተር ተዋናዮች ጭምር እያስጨነቃቸውና እንቅልፍ እየነሳቸው ነው፡፡ በቅርቡ በመንግስት በተካሄደ ግምት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በዚህ አመት ከ2 እስከ 3 ከመቶ ቅናሽ ያሳያል ተብሏል፡፡ ይህም ቅናሽ የሚከሰተው በዚህ አመት ከታቀደው የእድገት አሃዝ ላይ ነው ተብሏል፡፡ ቫይረሱ በአሁኑ ደረጃው እንኳን በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየሳየ ነው፡፡ ሁኔታው ካልተሻሻለ ደግሞ ኢኮኖሚው ይበልጥ እንደሚዳከም ግልፅ ነው፡፡ ሌሎችም ያልተገመቱ አለም አቀፍ ክስተቶች ሊፈጠሩና ችግሩን ሊያባብሱት እንደሚችሉ አንዳንድ ተንታኞች ያስጠነቅቃሉ፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው፣ መንግስትና የግሉ ሴክተር ባለፉት ዘመናት እምብዛም የሚግባቡ ሳይሆኑ እስካሁን ቢዘልቁም አሁን ግን ሁለቱም ያላቸው አማራጭ ኢኮኖሚውን ከውድቀትና ህዝቡን ከበሽታና ከከፋ ድህነት እንዲሁም ከእልቂት ለማዳን ወይ መተባበር አለበለዚያም ኢኮኖሚው ይበልጥ እንዲጎዳና ህዝቡ ከገባበት ጥልቅ የቀውስ ጉድጓድ እንዳይወጣ ማድረግ ይሆናል ቢባል ነገሩን ማጋነን አይሆንም፡፡

ማንም አገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ የሚል ወገን የመከራ መንገድ እንደማይመርጥ እንኳንስ እንደ ኢትዮጵያ ህዝቡ ከደስታ ጊዜ ይልቅ በችግር ጊዜ የሚተባበር መሆኑ ቀርቶ፣ ግለኝነት እጅጉን በሰፈነባቸው በምእራባውያን ህብረተሰቦች ውስጥ እንኳን የሚታሰብ ነገር አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ በበኩሉ ባለፈው ጊዜ ከመንግስት ጋር የሚገባውን ያህል መግባባትና አብሮ መስራት ባይችልምና በሆነ ባልሆነው ጥፋተኛ ተደርጎ ቢቀርብም፣ አሁን አገሪቷ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት ያለፈውን ሁሉ ረስቶ ወይም ችላ ብሎ አገርንና ህዝብ በማዳኑ አጣዳፊ ሁለገብ ተግባሮች ውስጥ ንቁና ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ የንግዱ ማህበረሰብ ለወገንና ለአገር ያልሆነ ጥሪት ለመቼ ይሆናል በሚል በእልህና በአገር ወዳድነት ስሜት በመነሳሳት ያለውን የሌለውን ሁሉ ለዚሁ ቅዱስ አላማ እያዋለው ነው፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ ሃብት ያፈራውም ሆነ ሰርቶ የሚበላው በዚች ድሃ አገርና ድሃ ህዝብ መሃል ስለሆነ አሁን ሁሉንም ወገን ሰንጎ የያዘው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ መፍትሄ እስካላገኘ ድረስ ስለትርፍና ስለ ሃብት ማካበት የሚያስብ አንድም የንግዱ ማህበረሰብ አባል ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከሁሉም በላይ አሁን አጣዳፊው ተግባር ህዝብንና አገርን አሁን ከሚታየውና ከሚመጣው መከራ መታደግ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም አገርና ህዝብ በጤናና በሰላም ሲኖሩ ነው ነግዶ ማትረፍም ሆነ ሃብት ማፍራት የሚቻለው፡፡

አለምን ከዳር እስከ ዳር በእሳት ነበልባል አጥር አጥሮ እያቃጠለ የሚገኘው የኮቪድ 19 የበሽታ በመንግስት ብቸኛ ጥረት ወይም በንግዱ ማህበረሰብ መዋጮ አለበለዚያም በሃብታም አገሮች እርዳታ የሚጠፋ አይደለም፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ እንኳንስ እንደኛ ያሉትን ድሃ አገሮች ቀርቶ በሃብትና በስልጣኔ፣ በቴክኖሎጂና በሳይንስ አንቱ የተባሉትን ከበርቴ አገሮች ሳይቀር ሱሪ አስፈትቶ አንበርክኳል፡፡ የሚይዙትን የሚጨብጡትን አሳጥቶ ህዝቦቻቸውን እንደ ቅጠል አርግፏል፡፡ በአሜሪካ በሁለት ወራት ብቻ አገሪቱ ብዙ አመታት በተዋጋችበት በቬትናም ጦርነት የጣችውን የሰው ቁጥር የሚበልጥ ዜጎቿን እንድታጣ አድርጓታል፡፡ የአውሮፓ ሆስፒታሎች የእሬሳ ማምረቻ ፋብሪካዎች መስለዋል፡፡ በአፍሪካም ቢሆን ከባዱ ጊዜ ወደፊት የሚመጣው ነው ተብሎ ስለሚገመት ያንን መጥፎ ጊዜ በፍርሃት የሚጠባበቁ ሰዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡

በአገራችንም ቢሆን ምንም እንኳን ወረርሺኙ በዝግታ እየተራመደም ቢሆን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማህበረሰቡ ውስጥ መሰራጨቱን የሚጠቁሙ ተጨባጭ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ ሲጀመር ከውጭ የመጡ ዜጎችን ብቻ ያጠቃው ቫይረስ አሁን ግን ማህበረሰቡ ውስጥ ገብቶ ፍጥነቱን እየጨመረ ይገኛል፡፡ በተለይም ህዝቡ ከመንግስትም ሆነ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክር በአብዛኛው ችላ በማለቱ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጠር በአያሌው እንደሚጨምር በጭንቀት የሚናገሩ ሰዎች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እነዚህን ሰዎች ይበልጥ የሚያስጨንቀው ደግሞ አገሪቱ ያላት የኢኮኖሚ አቅም ከወዲሁም ቢሆን እየተንገዳገደ የቆመ በመሆኑ የተፈራውን ቀውስ የማስቀረት አቅም የሌለው መሆኑ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንግዲህ መንግስትና የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ህዝቡ ያላቸው ብቸኛ የቀውስ መቋቋሚያ መሳሪያ ህብረታቸውና መተሳሰባቸው ነው፡፡ ነገዴው አገርንና ህዝብን ከወረርሺኙ ለማዳን ከወዲሁ የማያሳየው ተነሳሽነት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ገንዘባቸውን፣ ቤታቸውን፣ ፎቃቸውን፣ ድርጅታቸውንና ፋብሪካቸውን ወረርሺኙን ለመቋቋም ለሚውሉ እንቅስቃሴዎች መስጠታቸው አስገራሚ የሆነ የአገር ወዳድነት መገለጫ ነው፡፡ ነጋዴው ለአገሩና ለህዝቡ ይህን ያህል አስተዋፅኦ ሲያደርግ በመንግስት በኩል ደግሞ ድጋፍ ለደረግለት እንደሚገባ ግልፅ ነው፡፡

ብዙ የንግድና አምራች ተቋሞች በገንዘብ እጥረት ከመዘጋት ወይም ከኪሳራ የሚድኑበትን መንገድ መንግስት ማፈላለግ ይጠበቅበታል፡፡ የግብር ጫና ያለባቸው የግል ተቋሞች የግብር እፎይታ በአስቸኳይ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ይከፍሉት የነበረውም የግብር መጠን የሚቀነስበትን መንገድ መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ የመንግስተ እርምጃ የባንክ ብድር ከመስጠት እስከ እዳ ስረዛ ሊደርስ ይችላል፡፡ በተለይ አነስተኛ የንግድ ተቋሞች የወረርሺኙን ተፅእኖ ተሸክመው መዝለቅ ስለሚከብዳቸው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ መንግስት ከውጭ የገንዘብ ድርጅቶች በብድርም ሆነ በእርዳታ ከሚያገኘው ገንዘብ የተወሰነውን ለእንደዚህ አይነቶቹ ተቋሞች ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መንግስት ከተለያ አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ሊያገኘው ካሰበው ወደ 7 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዝብ ውስጥ ለውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከሚመድበው ውስጥ ለግሉ ሴክተር የሚገባውን ድርሻ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

አንዳንድ የግል ባንኮች ነጋዴዎች ተበድረው ከሰሩ በኋላ መክፈል ያለባቸውን ወለድ ለተወሰነ ጊዜ ወይም ጨርሰው እንዳይከፍሉ ማድረጋቸው በምሳሌነት የሚጠቀስ የትብብር እርምጃ ነው፡፡ መንግስትም ቢሆን በተጠና መልኩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የንግድ ተቋሞች በመለየት ተመሳሳይ ድጎማ ቢያደርግላቸው ውለታ መመለስ ሳይሆን ኢኮኖሚው እንዳይወድቅ ከሚደረጉት እርምጃዎች እንደ አንዱ ሆኖ መታየት ይኖርበታል፡፡

ኮቪድ-19 እጅጉን ከጎዳቸው ተቋሞች መካከል የሆቴልና የመስተንግዶው ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው የቱሪዝም ሴክተሩ ይገኝበታል፡፡ አያሌ ሆቴሎች ባዷቸውን ቀርተዋል፡፡ ቱሪስቶች ለጉብኝት ወደ አገራችን መምጣት አቁመዋል፡፡ አንዳንዶቹ አስጎብኚ ድርጅቶች እንዲያውም ለሰራተኞቻቸው ደምወዝ መክፈል እስከመቸገር ደርሰዋል፡፡ በዚህም ረገድ ስራቸውን መቀጠል ይችላቸው ዘንድ አስቸኳይ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከባንክ የተበደሩትን ከፍተኛ ገንዘብ በወቅቱ መመለስ ቀርቶ ድርጅታቸውን እስከመዝጋት ሊያደርስ የሚችል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ባለሃብቶች መሆናቸው ቀርቶ ባለእዳዎች ወደመሆን እየተሸጋገሩ ናቸው፡፡

እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ የንግዱን ህብረተሰብ ችግሮች ለመፍታት መንግስትና ነጋዴው ተቀምጠው መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡ እንደ ቀድሞው ጊዜ ሁለቱ ወገኖች በሩቅ እየተያዩ ወይም ለይስሙላ እየተገናኙ መተቻቸት ሳይሆን በተጨባጭና ጊዜ በማይሰጡ ችግሮች ዙሪያ መክረው አስቸኳይ መፍትሄ ማፈላለግ ለነገ የማይሉት ተግባር መሆን ይኖርበታል፡፡

አንድ አገር የውጭ ወረራን ተከትሎ ጦርነት ውስጥ በሚገባበት ወቅት ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የስማራል፡፡ ኮቪድ-19 ደግሞ ከጦርነት ሁሉ የከፋ ጦርነት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ነገር ወረርሺኙን ለመቋቋም ትግል ወደሚካሄድበት መድረክ መላክ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ሰው ተዋጊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሁሉም የኢኮኖሚ ሴክተር ለዚሁ ጦርነትና ድል መሰለፍ ይገባዋል፡፡ መንግስተና ህዝብ ደግሞ መደማመጥና እንደ አንድ ሰው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግስትና የኢኮኖሚው ዋልታ የሆኑት ነጋዴዎች ይበልጥ መደማመጥና ይበልጥ መቀናጀት ይገባቸዋል፡፡ የነዚህ ሁለት አካላት ተቀራርቦ መስራት ኮቪድ-19ን ለማሸነፍ አንዱና ዋነኛው መተማመኛ መሆኑ ከግልፅም በላይ ነው፡፡ ምናልባትም ወረርሺኙ ተሸንፎ ከሃገር ሲወጣ ጥሎልን የሚያልፈው መልካም ነገር ቢኖር ይሄው በመንግስትና በግሉ ሴክተር መካከል በመከራ ጊዜ የተገነባው ትብብር ሊሆን ይችላል፡፡