መንግስት ለቅመማ ቅመም ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

ኢትዮጲያ ለቅመማ ቅመም ምርቶች ልማት ምቹ መሬት እና የአየር ንብረት ያላት ቢሆንም መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጲያ የቅመማ ቅመም ሀመልማልና መአዛማ አምራቾችና አቀናባሪዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አዲሱ አለማየሁ ከኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት አትራፊ እና አዋጭ የሆነው የቅመማ ቅመም ዘርፍ በመንግስት በኩል በቂ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡
በመንግስት ፖሊሲ ማእቀፍ ውስጥ ሌሎች በሚለው መዘርዝር ውስጥ የተቀመጠው እና ቅድሚያ ያልተሰጠው የቅመማ ቅመም ዘርፍ በየአመቱ ሀገሪቱ ከኤክስፖርት ልታገኘው የምትችለውን ብዙ ሚሊዮን ዶላር እያሳጣት ነው ብለዋል፡፡ ዘርፉ ሊያካትታቸው የሚገቡ ምርቶች በተለያዩ መ/ቤቶች ስር መበታተናቸው ፤ አንዳንዶቹ ምርቶች ባለቤት የሌላቸው መሆናቸው ፤ የመሬት አቅርቦት ፤ የፋይናንስ ተቋማት በንድፈ ሀሳብ ላይ ያተኮረ ወይም ያለ መያዣ ንብረት የሚያስተናግድ የብድር አገልግሎት አለመኖር የዘርፉ ዋና ዋና ችግር መሆናቸውን አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡
ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ የመንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት መሆኑን ያነሱት አቶ አዲሱ ጠቃሚ የሆኑ እና በሚመለከታቸው መ/ቤቶች ተሰንደው ያሉ መመሪያዎች ከመደርደሪያ ወርደው ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጲያ በቅመማ ቅመም ትልቁን የኤክስፖርት ገቢ ያገኘችው እ.ኤ.አ በ2014 ሰሆን 33 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ መመዝገቡን ያስታወሱት አቶ አዲሱ ከዚህ ውስጥ 24 ሚሊዮን ዶላር ያስገኝ የነበረው ዝንጅብል ምርት ላለፉት 8 አመታት ኤክስፖርት ተደርጎ አይታወቅም ብለዋል፡፡
በወቅቱ ዝንጅብልን የሚያጠቃ በሽታ ተከስቶ ነበር ያሉት አቶ አዲሱ ሌሎች ሀገራት ይህንን ተቋቁመው ሲያልፉ በኢትዮጲያ ውስጥ ግን ይህ ባለመሆኑ ሀገሪቱ ዝንጅብልን ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ከውጭ እንደምታስገባ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም መንግስት ለዚህ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እንዲሁም የተሰሩ ጥናቶችንም እንደ ግብአት ወስዶ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንድታመነጭ መስራት እንዳለበት አቶ አዲሱ አሳስበዋል፡፡
በቴሌግራም ፡- https://t.me/ETIradioshow
ቤተሰብ ይሁኑን እናመሰግናለን