ምክር ቤቱ ለዩኒቨርሲቲ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች የሥራ ልምምድ እድል ሰጠ

ዓላማውን አስመልክቶ  የም/ቤቱ ሀላፊዎች ለተመራቂ ተማሪዎች ባደረጉት ገለፃ  ም/ቤቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ባደረገው ስምምነት  በአመቱ መጨረሻ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የምክር ቤቱን አገልግሎቶች ለማስተዋወቅና አዳዲስ አባላትን የመመልመል ስራ ላይ እንዲሣተፉ በማድረግ  ምሩቃኑ በትምህርት ዓለም የገበዩትን  የንድፈ-ሀሳብ እውቀት  ተግባር ላይ የሚያውሉበትን  እድል በማመቻቸት በሥራ ዓለም ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ምክር ቤቱ ማህበራዊ ሃላፊነቱንም በዚህ መልክ እንደሚወጣም አንዱ ማሳያ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ተለማማጅ ተማሪዎቹ ከቅድስተማርያም  ፣ ከሆፕ ፣ከኒዉ አቢሲኒያ እና ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ  የተውጣጡ ናቸው  ::

የም/ቤቱ ሽያጭ ወኪሎችም በሥራ ዘመናቸው ያካበቱትን ልምድ ለተሳታፊ ምሩቃን አካፍለዋል::  ምሩቃኑም ከምክር ቤቱ ጋር  ስምምነት ፈርመው እና አስፈላጊው ሰነድ ተዘጋጅቶላቸው ስራ የጀመሩ ሲሆን ፣  የምክር ቤቱ የአባላት ጉዳዮች መምሪያ ለተመራቂዎቹ ክትትል እና ድጋፍ  በመስጠት በየጊዜው ሪፖርት እንሚያቀርብ ታውቋል፡፡

በሆፕ ዩኒቨርሲቲ የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተማሪ  የሆነችው ታሪኳ በላይ   ስልጠናውን ከተከታተሉት ወጣቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ የሽያጭ ሥራ ማለት ወንበር እና ጠረጴዛ ሊገዛ የመጣን ደንበኛ አሳምኖ ሶፋም ጨምሮ  እንዲገዛ ማድረግ  ማለት ነው ትላለች፡፡ በእኔ አመለካከት አለማችን  በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ  እና ውስብስ እየሆነ የሚሄድ  የንግድ ሥርዓት ውስጥ ትገኛለች፡፡  እደዚህ ዓይነቱ  ልዩ ሥልጠና  ከትምህርት ቤት ይልቅ የገሃዱ ዓለም ላይ ያለውን ተጨባጭ የንግድ ሥርዓት፤ ያሉትን ተግዳሮቶች በተግባር እንድንመለከት ይረዳናል በሚል ታስራዳለች፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ይህንን እድል በነፃ ስላመቻቸልን አመሰግናለሁ ብላለች፡፡

የአባላት ጉዳዮች መምሪያ ሥ/አሥኪያጅ ወ/ሮ ገነት ዘነበ  በበኩላቸው ፕሮግራሙ ተመራቂ ተማሪዎች የንግዱን ዓለም እንዲያውቁት እና የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው የሚያግዝ በመሆኑ ም/ቤቱ ይህንን ፕሮግራም በተከታታይ  በየዓመቱ በክረምት ወራት ለማከናወን እቅድ ይዟል ብለዋል፡፡