በሃገራዊ ምክክሩ የግሉ ዘርፍ በንግድ ምክር ቤቶች በኩል መወከል አንዳለበት ተገለጸ::

የአዲስ አበባ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኢኒሼቲቭ አፍሪካ ጋር በመተባበር በመጭው ሃገራዊ ምክክር ላይ የግሉ ዘርፍ ሚናን አስመልክቶ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
የግሉ ዘርፍ በሃገራዊ ምክክሩ ዋና ተዋናይ መሆን እንዳለበት አጽንኦት በተሰጠበት የውይይት መድረክ ላይ ከብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም ኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅቱን በመጨረስ ወደትግበራ ለመግባት ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል ።
የተሳታፊዎች ልየታ ተጠናቆ ሲያልቅ አጀንዳዎች ለኮሚሸኑ እንደሚልኩም ገልጸዋል::
በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ ያለውን የገንዘብ የእውቀት እና የቁሳቁስ አቅም ድጋፍ እንደሚያደርግ እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የኮሚሽኑ የመጀመርያው መርህ አካታችነት መሆኑን ተከትሎ ይህን ማሳካት እንዲቻል መሰል ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
በመድረኩ ለውይይት መነሻ የሚሆን ልምዳቸውን ካካፈሉት መካከል በውጭግንኙነት ስራዎች ልምድ ያላቸው ድ/ር አብደታ ድርብሳ አንዱ ሲሆኑ ከሌሎች ሃገሮች ተሞክሮ በመነሳት ኮሚሽኑ ሁሉን ለማስታረቅ የሚሆን ማእቀፍ ያለው እና እምነት የሚጣልበት መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ከዚህም አንጻር አካታችነት እና ቁርጠኝነት አለመኖር ምክክሩ ካልተሳካባቸው ሀገሮች የተገኙ ልምዶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ወ/ገብረኤልም ንግድ መንቀሳቀስን ፍትህን የሚፈልግ እንደመሆኑ የምክክሩ አስፈላጊነት ወሳኝ መሆኑን አንስተው የንግዱ ማህበረሰብ በምን መልኩ ይወከል የሚለው ትኩረት የሚፈልግ እንደሆነ ተናግረዋል::
አክለውም መንግስት በሀገራዊ ምክክሩ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ እና በልኩ አስትዋጽኦ እንዲያበርክት ከተፈለገ በአዋጅ የተቋቋሙ የንግድ ምክር ቤቶችን በዋናነት ማሳተፍ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል::
ይህ ካልሆነ ስኬታማ ምክክር ለማድረግ እንቅፋት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *