በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ከአዲስ ቻምበር አመራሮች ጋር የሁለቱ አገራት ንግድን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መከሩ ፡፡

በኢትዮጲያ የቼክ አምባሳደር ሚሮሰላቭ ኮሴክ ከአዲስ ቻምበር የቦርድ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሽንቁጤና ፣ ከዋና ፀሀፊው አቶ ሺበሺ ቤተማርያም ጋር በምክር ቤቱ የቦርድ መሰብሰቢያ አዳረሽ የሁለቱ አገራት ነጋዴዎች ተጠቃሚ መሆን በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል ፡፡

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ሚሮሰላቭ ኮሳክ ፤ ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትየጵያ ጋር በንግድና እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በባህል መልካም የሚባል ግንኙነት አላት ብለዋል ፡፡

የቼክ ኩባንያዎች በጤናው ዘርፍ ፣ በግብርና ፣ በምግብ ማቀነባበር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ መዋለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ማፍሰሳቸውን አንስተዋል ፡፡

አክለውም ሀገራቸው ቡና ፣ እና አበባ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን እንደምታስገባ ጠቅሰው ፤ በተለይ ቡና ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል ፡፡

የአዲስ ቻምበር ፕሬዝዳንት ወ/ ሮ መሰንበት ሽንቁጤ በበኩላቸው ኢትዮጰያና ቼክ ሪፐብሊክ ጠንካራ የሚባል ግንኙኘነት እንዳላቸው ጠቅሰው በኮቪድ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የንግድ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ ኤምባሲው እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል ፡፡
አዲስ ቻምበርም የንግድ ግንኙነቱ ዳግም ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል ፡፡

የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በበኩላቸው ባለፉት ዘመነ መንግስታት ቼክ በመከላከለያ ዘርፍ ፣ በህክምና ፣ በምግብ ማቀነባበር፣ በድልድይና መሰል የግንባታ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አስተዋፆ ነበራት ብለዋል፡፡

በአውሮፓዊያኑ ከ2013 እስከ 2018 ድረስ በነበረ ፕሮጀክት አማካኝነት ጠንካራ ግንኙነት በመመሰረት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ከኢትዮጵያ እንድትገዛ መደረጉን ገልፀዋል ፡፡

የቼክ ኩባንያዎች በተመረጡ ዘርፎች ማለትም በማዕድን ፣ በአውቶሞቲቪ ኢንዱስትሪው ፣ በግብርናው እና በቢራ መጠጥ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበራቸው ብለዋል ፡፡

በቼክ ኢምባሲ የንግድ አታሼው ፓቬል ሳር በበኩላቸው ግንኙነቱን ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ የቼክ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት የቼክ- አፍሪካ የንግድ ጉባኤ የፊታችን ሚያዚያ እንደሚካሄድ አስታወቀዋል ፡፡

በአውሮፓዊያኑ ከሚያዚያ 26 – 27 /2023 በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የአፍሪካ አገራት ንግድ ምክር ቤቶች አሁናዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችና የንግድ እድሎችን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው ብለዋል ፡፡

በተጨማሪም ነጋዴዎች በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ የቼክ ኩባንያዎች ጋር ተገናኝተው በጋራ ሊሰሩ የሚችሉበትን መንገድ የሚያመቻቹበት የንግድ ለንግድ ውይይትም ይካሄዳል ብለዋል ፡፡

ይህም ለኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች አዳዲስ አጋሮችን ለማግኝት መልካም እድል የሚፈጥር በመሆኑ ንግድ ምክር ቤቱ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡edited 15:36

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *