ብዙ የሚቀረው የሴቶች መብት ጉዳይ

በሕዝብ፤መንግሥታዊ ባልሆኑ እና በግል ኩባንያዎች ጭምር በሥራ ቦታዎች አካባቢ የሥርዓተ ጾታ ክፍሎች ማየት እየተለመደ መጥቷል ፡፡

በየጊዜው በመገናኛ ብዙኃን እና በትምህርት ቤቶች ወዘተ አማካኝነት በሴቶች ላይ ስለሚደርሱ ጥቃቶች እና መከላከልያ ዘዴዎችን አስመልክቶ ትምህርቶች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየተሰጡ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ተደማምሮ በተለይ በሥራአካባቢ ላይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ትንኮሳዎች እና ጥቃቶች እየቀነሱ ነው ተብሏል፡፡

የሴቶች በሥራ ቦታዎች ላይ ከሚደርስባቸው በደል ለመከላከል በሚያስችሉ ሁኔታዎቸ ላይ ለመወያየት በተጠራው የምክክር መድረክ የአዲስ ቻምበር ፕሬዝደንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ ባሰሙት ንግግር መንግሥት ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከልና መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ የተለያዩ ጥረቶች እየደረገ ነው፡፡

ከጥቂት አመታት ወዲህ የታወጁት እንደ የቤተሰብ፤ የሠራተኞች እና የሲቪል ሰርቪስ የመሳሰሉት አዋጆች የሴቶችን ማሕበራዊ፤ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች እና ጥቅሞች ከማስጠበቅ አንጻር ውጤት አስገኝተዋል፡፡

በሕብረተሰቡ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥም እየመጣ ነው ብለዋል፡፡

ነገር ግን አሁንም ቢሆን ሴቶች በሥራ ገበታቸው ላይ እየሉ ጾታ-ተኮር ጥቃቶች እየተፈጸሙባቸው እንደሆነ በየጊዜው ይሰማል ፡፡

በተለይ ሴቶች በሚበዙበት አንደ ጨርቃጨርቅ እና ሰፋፊ እርሻዎች ባሉ የሥራ ቦታዎች በሴቶች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ይፈጸምባቸዋል፡፡

ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት አንስቶ ለንግዱ ሕብረተሰብ የተለያዩ ትምህርታዊ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ በምክር ቤቱ አባል ኩባንያዎች ዘንድ የሴቶች የሥራ አካባቢ መብት አጠባበቅ እና እንክብካቤ አስመልከቶ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎች እየሰጠ ነው ሲሉ ፕሬዝንደቷ ገልጸዋል፡፡

ከአበባ አምራቾች እና ላኪዎች ማሕበር የመጡት ወ/ሮ ዮዲት ግርማ በበኩላቸው ሴቶች ካላቸው ሕዝብ ብዛት ድርሻ እና ከችግሩ ስፋት አንጻር ስለ ሴቶች መብት አጠባበቅ ብዙ መሥራት ይቀራል ፡፡

ማሕበራቸው ወደ 65 በሚጠጉ እርሻዎች የሚሰሩ እና ቁጥራቸው ከ200 ሺኅ በላይ የሚሆኑ ሴቶችን ከጥቃት ለመታደግ ሲል አንድ ወጥ የሥርዓተ-ጾታ ፖሊሰ አዘጋጅቶ በአባላቱ እንዲተገበር እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በእያንዳንዱ እርሻ ጣቢያ የሴቶችን መብት እና ጥበቃ የሚከታተሉ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ቁጥጥር እያደረጉ ነው፤ ማሕበራቸውም ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል ፡፡

በአገር ደረጃ ፖሊሲ አለመኖር ከችግሩ አንኳር ምክንያቶች አንዱ ያሉት ወ/ሮ ዮዲት በተለይ በገጠር አካባባዎች ችግሩ ታዳጊዎችን ጭምር የሚነካ አንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከሴቶች እና ሕጻናት ጉዳይ ሚ/ር የተወከሉት ወ/ሮ ሕሊና ላቀው በበኩላቸው የሴቶችን የሥራ ቦታ ላይ ከጥቃት የሚከላከል ፖሊሲ መ/ቤታቸው አዘጋጅቶ ረቂቁን ለፕላንና ልማት ኮሚሽን ማቀረቡን ገልጸው ፖሊሰው ጸድቆ እንደመጣ መ/ቤታቸው ፖሊሲውን ለመተግበር ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ከዴንማርክ ኢንዱስትሪዎች ኮንፌዴራሲዮን የመጡት ክላራ ሃልቮርሰን በአገራቸው ስላለው የሴቶች ማሕበራዊ፤ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶ አጠባበቅ ሥርዓት ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በተለይ በግል ኩባንያዎች ዘንድ የሴቶች የሥራ ላይ መብቶች እና ጥበቃ አስተማማኝ እና ዘላቂ አንዲሆን የኩባንያ ባለቤቶች ገዢ የሆነ የቃልኪዳን ሰነድ ይፈርማሉ፡፡

በአገሪቱ ለሴቶች መብት እና ጥበቃ የወጡ የተለያዩ ሕግጋት አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ኮንፌዴራሲዮኑ የሚያስተገብረው እና የሚከታተለው የቃልኪዳን ሕግ ሴቶች በሥራ ላይ በራሳቸው አንዲተማመኑ እና አሰተዳደራዊ አድልዎ እንዳይደርስባቸው ዋስትና የሚሰጥ ነው ሲሉ ያገራቸውን ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡

ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች እና አሰተያየቶች ቀረቡ ሲሆን በአቅራቢዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *