ንግድ ምክር ቤቱ የሜንቶር ሺፕ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

በውጪው ዓለም የሚውለው እና በሰፊው ተቀባይነት ያለው የሜንቶርሺፕ ወይም የማማከር እና ልምድን የማጋራት አገልግሎት ልምድን ለተተኪዎች በማካፈል ውጤት ማምጣት የሚቻልበት አሰራር ነው፡ይሁን እና በሃገራችን አሰራሩ ብዙም ያልተለመደ ከመሆኑ አንጻር በንግድ ውስጥም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ጀማሪዎች አቅጣጫ የሚያሳያቸውም ሆነ ልምድ የሚያካፍላቸው ለማግኘት ሲቸገሩ ይስተዋላል ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትም የንግድ ስራን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለአባላቶቹ ያቀርባል፡፡ ከአገልግሎቶቹ ውስጥም በየደረጃው የሚገኙ ነጋዴዎች ፤አምራቾች እንዲሁም ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎችን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የስልጠና ድጋፎችን ፡የንግድ ለንግድ ግንኙነት እድሎችን እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ ንግድ ነክ መረጃዎችን በመስጠት አወንታዊ ሚናውን በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡
ምክር ቤቱ የሜንቶር ሺፕ አገልግሎት ውጤታማ ንግድን ለማከናወን የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት በንግድ እንቅስቃሴ ረዘም ያለ ልምድ ያለቸውን ፈቃደኛ የምክር ቤቱ አባላትን በመለየት ልምዳቸውን ለሌሎች የሚያካፍሉበትን እድል ፈጥሯል፡፡
የምክር አገልግሎቱን የሚያገኙት በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች ሲሆኑ በየተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ ላይ በንግድ ስራ፤በአምራችነት እንዲሁም በማማከር የስራ ዘርፍ ውስጥ የቆዩ እና በአመራር ብቃታቸው ውጤታማ የሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ተመድበውላቸዋል፡፡ በሌሎች ሃገራት የሚንቶርሺፕ አገልግሎት ለአንድ አመት እንዲቆይ ተደርጎ ይቀረጻል ፡ይሁን እና ምክር ቤቱ ያዘጋጀው የሜንቶርሺፕ አገልግሎት ለስድስት ወር የሚቆይ ሲሆን ውጤቱም እየታየ እንዳስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችል እና ቀጣይነት እንዳለውም የምክር ቤቱ የንግድ ድጋፍ መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ፍቅርተ ልጅአለም በስነስርዓቱ ላይ ገልጸዋል ፡፡
አገልግሎቱን የሚያገኙት ነጋዴዎች የኤክስፖርት ልምዳቸውን ለማዳበር፡እንዲሁም በአምራች ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆኑ ፤ የራሳቸው እቅድ እና ግብ አስቀምጠው እንዲንቀሳቀሱ የምክር አገልግሎቱ እንደሚረዳቸውም ገልጸዋል፡፡