አዲስ ቻምበር እና የኢት. ዜና አገልግሎት ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሚያስችል የመግባቢያ ሠነድ ተፈራረሙ::

በአዲስ ቻምበር እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሠነድ ሁለቱ ተቋማት  ዓላማዎቻቸውን ለማሳካት ትልቅ ድርሻ እንዳለው በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ ተነግሯል፡፡

የንግድ ም/ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም  እንደተናገሩት ምክርቤቱ የግሉን ዘርፍ  ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የሚዲያ ተቋማት በተለይም ኢዜአን ከመሳሰሉት ጋር በጋራ ይሰራል ፡፡

አዲስ ቻምበር  ለአባላቱ እና ለመላው የንግድ ሕ/ሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲሁም የሚሰራቸውን የፖሊሲ አድቮከሲ ሥራዎችን   የበለጠ ተደራሽ አንዲሆኑ  ከዜና አገልግሎቱ ጋራ በትብብር መሥራት ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚ  አቶ ነጋሲ አምባዬ  በበኩላቸው  ዜና አገልግሎቱ በዋናነት የአገር ገጽታ ግንባታ እና የኢኮኖሚ ልማት ማስፋፋት   በመሆኑ  በምክር ቤቱ የሚዘጋጁ የቢዝነስ እና ንግድ ነክ መረጃዎች የጥናት ውጤቶች  የድርጅታቸውን ሥራ  የተሟላ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ዜና አገለግሎቱ በምሥራቅ አፍሪቃ ተጽዕኖ ፈጣሪ  የመረጃ ምንጭ ለመሆን ራዕይ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት በቢዝነስ ማስፋፊያ ፤በአቅም ግንባታ እና  በሌሎች  የጋራ አጀንዳዎች   ላይ በጋራ አንደሚሰሩ  ከስምምነቱ ሠነድ ለመረዳት  ተችሏል፡፡

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረመ።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸኃፊ አቶ ሺበሺ ቤተ-ማሪያም ፈርመውታል።

ሥምምነቱን በተለይም ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያሳልጡ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራትና ምክር ቤቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት የበለጠ ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

ተቋማቱ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ የሚደጋገፉ ሲሆን ቶክሾውና ውይይቶችን በማዘጋጀት፣ በጥናትና ምርምር ተግባራት ላይ የሚተባበሩ መሆኑንም በሥምምነቱ ላይ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸኃፊ አቶ ሺበሺ ቤተማሪያም እንደገለጹት ምክር ቤቱ ከተለያዩ አገራት ጋር የንግድ ግንኙነቶችን ማድረግ፣ የንግድ ትርኢቶች ማካሄድ፣ በውጭ አገራት ፎረሞችን ማከናወንን ጨምሮ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ያካሂዳል።

ከዚህ ባሻገርም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑና ጥናት ላይ የተመሰረቱ አውደ ጥናቶች፣ ሴሚናሮችና ጉባኤዎች ምክር ቤቱ እንደሚያካሂድ ጠቁመው እነዚህ ሁሉ ሥራዎች በአግባቡ በመገናኛ ብዙኃን በሚጠበቀው ደረጃ ተደራሽ እየሆኑ አይደለም ብለዋል።

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የረጅም ዓመታት ልምድ ካካበተው ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በጋራ መሥራቱ ሁነኛ መፍትሄ ነው ሲሉ አክለዋል።

ምክር ቤቱ በቀጣናው የንግድ ትስስርን ማሳለጥ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡ ሥምምነቱ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ዘመናዊ አሰራር የሆኑት እንደ ካፒታል ገበያ ላይ ምክር ቤቱ በስፋት ለመሥራት ውጥን እንዳለው የገለጹት አቶ ሺበሺ በዚህ በኩል ከኢዜአ ጋር አብረን መስራታችን ጉዞውን የተቃና ያደርገዋል ነው ያሉት።

የምክር ቤቱ ዋና ጸሃፊ ልዩ አማካሪ አቶ ሲሳይ ታደሰ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ከኢዜአ ጋር በትብብር መሥራቱ የግሉ ዘርፍ ማነቆዎች እንዲፈቱ ማድረግ ላይ አዎንታዊ አሻራ የሚያሳርፍ መሆኑን ተናግረዋል።

በሥምምነቱ ማዕቀፍ ላይ የተቀመጡ ጉዳዮች ወደ መሬት እንዲወርዱ ምክር ቤቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነጋሲ አምባዬ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት የፈረሙት ሥምምነት ንግድና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት ረገድ ያለው ፈይዳ ከፍ ያለ መሆኑ ጠቅሰዋል።

“ኢኮኖሚው ሲያድግ የገጽታ ግንባታውም በዛው ልክ ይጨምራል” ያሉት አቶ ነጋሲ የገጽታ ግንባታና የኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚያፋጥኑ ተግባራትን በጋራ ለመከወን ተስማምተናል ብለዋል።

ኢዜአ ዜናዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከበርካታ መገናኛ ብዙሃን ጋር ሥምምነት መፈረሙን አስታውሰው ምክር ቤቱ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች የበለጠ ለማስተዋወቅና ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ወንድራድ እንደገለጹት ተቋማቱ ያደረጉት ሥምምነት የግልና የመንግሥት አጋርነትን የማጠናከር ሚናው የላቀ ነው።

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በሥሩ በርካታ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች መኖራቸውን ጠቁመው ከዚህ አንጻር ሥምምነቱ በከተማው ብሎም በአገሪቱ ያሉ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *