አዲስ ቻምበር ከአዳማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ ፡፡

ስምምነቱን የሁለቱ ንግድ ምክር ቤት ዋና ፀሀፊዎች በአዲስ ቻምበር የቦርድ መስብሰቢያ ዛሬ ሃምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ተፈራርመዋል ፡፡

የአዲስ ቻምበር ዋና ፀሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያም ስምምነቱ በንግድ ምክር ቤቶች ብቻ ሳይታጠር የሁለቱ ከተሞች ስምምነት አድርገን ልናየው ይገባል ብለዋል ፡፡

አክለውም በንግድ ስራና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ያሉ ስራዎችን በጋራ ለመስራት መዘጋጀት ከሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የንግድ ምክር ቤቶች በቅንጅት መስራት ላይ ውስንነት እንዳለበቸው የጠቀሱት አቶ ሺበሺ ፤የግል ዘርፍ አጋርነት ( አሊያንስ) ለመፍጠር ምክር ቤታቸው እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

በኬኒያ የግሉ ዘርፍ ህብረት እንዳለ ጠቅሰው በኢትዮጵያም ሁሉንም ንግድ ምክር ቤቶች አቅፎ የሚያንቀሳቅስ መሰል የግሉ ዘርፍ ጥምረት አሰፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል ፡፡

ይህ ስምምነት ከዚህ አንጻር የላቀ ጠቀሜታ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልፀዋል ፡፡

ከአዳማ ንግድ ምክር ቤት ጋር ስምምነት ስናደርግ የመጀመሪያችን አይደለም ያሉት አቶ ሺበሺ አስራ ስምንት የመግባቢያ ሰነዶችን ከሌሎች ንግድ ምክር ቤቶችና ከመንግስት ተቋማት ጋር መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

የአዳማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሀፊ አቶ ሃጂ ከተማ በበኩላቸው ምክር ቤታቸው ከአዲስ ቻምበር ጋር ለመሰራት የወሰነው ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት በመሆኑና ብዙ የሚማሩበት ንግድ ምክር ቤት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሁለቱ ንግድ ምክር ቤቶች የተፈራረሙት ስምምነት በምርምርና የአድቮኪሴ ስራዎችን ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ፣ በንግድ ትርዒት ዘርፎች ላይ በጋራ ለመሰራት የሚያስችላቸው ነው ሲሉም ጠቅሰዋል ፡፡

ንቁና የበቃ ነጋዴ ለመፍጠር የሚያግዙ ሰልጠናዎች ከመሰጠት ባሻገር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ምክር ቤታቸው እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሃጂ ፡፡
ይሁንና አዲስ ቻምበር የተደረጃ አቅምና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንዳሉት ጠቅሰው በጋራ መሰራታቸው ንግድ ምክር ቤታቸውን ተጠቃሚ ያደርገዋል ብለዋል ፡፡

አዲስ ቻምበር ትልልቅ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ አንጋፋ ንግድ ምክር ቤት መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ቦርድ ፕሬዝዳንትና የአዳማ ንግድ ምክር ቤት የቦርድ አባል አቶ አበበ በንቲ ናቸው ፡፡

ከአዲስ ቻምበር ትልቅ ትምህርት ማግኝታቸውንና በቀጣይም በመደጋገፍ በመስራት ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ስምምነቱ ትልቅ እገዛ እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *