የቤት ግብር ተመን ማሻሻያው በአተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ገለጹ::

ከማሻሻያው በፊት የነበረው የክፍያ መጠን እዚህ ግባ የማይባል እና የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ የማያንጸባርቅ እንደነበር የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በበኩሉ አስታውቋል፡፡

በከፍያለው ዋሲሁን *

ይህ የተባለው አዲስ ቻምበር የቤት ግብር ማሻሻያ ላይ የግንዛቤ ማሰጨበጫ መድረክ በሚል በካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው ፡፡

የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ባቀረቡት ገለፃ እየተገለገልነበት ያለው አዋጅ በ1968 ዓ.ም የወጣውና አዋጅ ቁጥር 80 በመባል የሚታወቀው የከተማ ቦታ ኪራይና የቤት ግብር በመባል የሚታወቀው እንደነበር ጠቅሰዋል ፡፡

ነገር ግን ከተማዋ ቀድሞ ያልነበሩ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፣ ቪላ ቤቶችና ሪል ስቴቶች ጋር በተያየዘ አዋጁ በክፍያው ላይ ወቅታዊ በማድረግ ረገድ ከፍተት ያለበት መሆኑን አንስተዋል ፡፡

ይህም ከከተማዋ እድገትና አሁን ካለንበነት የመሰረተልማት ፍላጎትና እድገት ደረጃ ጋር አብሮ የሚራመድ ግብር መሰብሰብ አልተቻለም ያሉት አቶ አደም ፤ በዚህም ምክንያት በከተማዋ ማህበረ-ኢኮኖሚ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ላይ ውስንንነት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል ፡፡

አክለውም በቀደሞው አዋጅ ‹‹የጣሪያና የግድግዳ ግብር ከሚከፍሉ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል 96 በመቶ የሚሆኑት ከአምስት መቶ ብር በታች ይከፍሉ ነበር ›› ብለዋል ፡፡

ይህም ገንዘብ ለልማት ሊውል ቀርቶ የመሰብሰቢያንም ወጭ የሚሸፍን አልነበረም ሲሉ ግለፀዋል ፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ ሮ መሰንበት ሽንቁጤ ግብር ለከተሞች እድገት የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

ሆኖም በግብር ዙሪያ የሚወጡ አዋጆችና ደንቦች ከመውጣታቸው በፊትም ሆነ ከወጡ በኃላ የሚመለከታቸውን አካላት ሲያሳተፉ አይታይም ያሉት ወ/ሮ መሰንበት ከዚህ አንፃር ክፍተት እንዳለ አንሰተዋል ፡፡

በመሆኑም ንግድ ምክር ቤታቸው የግንዛቤ ማሰጨበጫ መድረኮችን በማመቻቸት መንግስትና የግሉ ዘርፍ ቀርበው እንዲመክሩ መድረክ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል ፡፡

ይህም በግብር ጉዳዮች ላይ መተማመን እንዲኖር እና ችግሮችም ካሉ ለመቅረፍ መንግስት የሚጠበቅበትን ገቢ እንዲሰበሰብ ያስችላል ብለዋል ፡፡

የአዲስ አበባ የንብረት ግብር ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አስማማው ሙሉጌታ በበኩላቸው የቤት ግብር አከፋፋል ላይ እሴትን ያገናዘበ ወቅታዊ ተደረገ እንጂ አዲስ አዋጅ አልወጣም ብለዋል ፡፡

በከተማዋ ከ285 ሺ በላይ ግብር ከፋዮች እንዳሉ ጠቅሰው ከተማዋ የምትሰበሰበው ግብር ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር አነሰተኛ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

ናይሮቢ ከአጠቃላይ ግብር ውስጥ የቤት ግብር 20 በመቶ ሲሆን ፣ የዛምቢያዋ ዋና ከተማ ሉሳካ 74 በመቶ እንደሚሰበሰቡ ለማሳያነት አቅርበዋል ፡፡

ይሁንና አዲስ አበባ ከተማ የምትሰበሰበው ከ1 በመቶ በታች 0 .08 መሆኑን አንስተዋል ፡፡

የአዲስ ቻምበር የግልግል ተቋም ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ወ/ገብርኤል ባቀረቡት የህግ ምልከታ በአዋጅ የወጣ የግብር ተመን ማሻሻያ የሚሻሻለው በአዋጅ ነው ሲሉ ሞግተዋል፡፡

በህግ የወጣ የግብር ተመን ማሻሻያ የሚሻሻለው በህግ ነው::

አዲስ ደንብም ሲወጣ በደንብ ይተካል ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ያሬድ ሀይለ መስቀል በበኩላቸው ይህ የቤት ግብር ተመን ማሻሻያ ወቅቱን ያላገናዘበ እና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ነው ሲሉ ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ አንጻር ሞግተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው ግብር መክፍሉን አንደግፋለን ነገር ግን አሁን ያለውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ታሳቢ ያደረገ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል ፡፡

በተጨማሪም የመከፍል አቅም የሌላቸው ዜጎች መክፍል አይችሉም እና እነርሱስ እንዴት ይታያሉ የሚሉ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተዋል፡፡

ህብረተሰቡ ላይ ተደራራቢ ችግር እንዳለ እንረዳለን ያሉት አቶ አስማማው ሆኖም የቤት ግብር ትመናው በጥናት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው የመክፍል አቅም የሌላቸው ባለቤቶች መክፍል እንደማይችሉ ከተረጋገጠ ለአንድ አመት ከከፍያ ነፃ የሚሆኑበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል ፡፡

የአምልኮ ቦታዎች ፣ ኢምባሲዎች ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የቤት ግብር ማሻሻያው የማይመለከታቸው መሆናቸውን የንብረት ግብር ማስተባባሪያ ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል ፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ እንዲህ አይነቱን የአድቮኬሲ የምክክር መድረክ በቀጣይ ጊዜያትና በወቅቱ ለአባላቱ የሚያዘጋጅ እንደሆነ ገልጿል፡።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *