የአክሲዮን ገበያ በኢትዮጲያ !!

የአክሲዮን ገበያ ጥንስስ በኢትዮጲያ ተጀመረ የሚባለው በአፄ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት በ1960ዎቹ አካባቢ እንደነበር ድርሳናት ያስረዳሉ ፡፡
በ1963 አ፣ም የተመሠረተው የአዲስ አበባ የአክሲዮን ንግድ ማኅበር፣ ከግብጽ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛው እንደነበርም ይገነገርለታል፡፡
ያኔ በብሔራዊ ባንክ አደራጅነት የተመሠረተው ‹‹የአዲስ አበባ ሼር ዲሊንግ ግሩፕ›› በወቅቱ አገር በቀል የነበሩ የአክሲዮን ኩባንያዎች የአክሲዮን ይዞታቸውን በስፋት የሚሸጡበት ማዕከል ከመፍጠር በተጨማሪ፣ የተለያዩ የአክሲዮን ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎችንና ደረጃዎችን ማጎልበት መቻሉ ይነገራል፡፡
በተለይ የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመምጣቱና አብዛኛው የግል ዘርፍ ተዋናዮች ከመክሰማቸው በፊት፣ በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የሚባሉ ኩባንያዎች ሳይቀሩ ባለአክሲዮን እንደነበሩ የግማሽ ምእተ አመት ትውስታ ነው፡፡
ለአብነት እንደ አዲስ አበባ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቄራዎች ድርጀት፣ ጠርሙስ ፋብሪካ፣ ኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኩባንያ፣ ኤችቪኤ ኢትዮጵያ፣ ተንዳሆ እርሻና ሌሎች እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 1974 ባለው ጊዜ ውስጥ አክሲዮን የሸጡ ኩባንያዎች እንደነበሩ ይገለጻል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ የግሉ ሴክተር በፍጥነት በማደግ ላይ የነበረ ሲሆን፣ ኩባንያዎችም አክሲዮኖችን ለሕዝብ በመሸጥ ካፒታል ያመነጩ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው የአክሲዮን ገበያ የተጧጧፈ ሲሆን፣ የአክሲዮን ግዥና ሽያጭም የወቅቱ ጉልህ የንግድና የማኅበራዊ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ የወታደራዊው ደርግ ዘመን አብቅቶ በኢሕአዴግ ዘመንም ቢሆን ይህ ጉዳይ ችላ ተብሎ የቆየ ሲሆን በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ እንድታደራጅ መወሰኑ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
የአክሲዮን ገበያ ተቋማዊ ሰርዓት የተበጀለት ፤ህዝብ የሚተማመንበት በመሆኑ በተለይ እንደ አሜሪካን እንግሊዝና ካናዳን የመሳሰሉ አገራት ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ለአኮኖሚያቸው አጋዥ ሞተር ሆኖ አገልግሏል ማለት ይቻላል ፡፡
ከፍተኛ የካፒታል አቅም በመፍጠርም ለግሉ ዘርፍ ምጣኔ ሃብት የገንዘብ ፍሰትን በማሻሻል፣ በቀላሉ ወደ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል ሃብትን በመፍጠር ባለሃብቱና ባለድርሻው ትርፍም ሆነ ኪሳራቸውን በጋራ እንዲጋሩ የሚያደርግ ስርአት ነውና አዎንታዊ ተጽእኖ ያመጣል የሚል እምነት አለ፡፡
በተለይ የገንዘብ ጉድለት ወይንም እጥረት ላለባቸው የኢንቨስትመንት መስኮች ገንዘብ በመደልደል አገራዊ ሃብትን በማሳበሰብ ቀጥተኛ የውጭ ንግድን በመሳብ ለአገር ምጣኔ ሃብት እድገት ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ሁላችንም እንገነዘባለን።
ሀገራትም የአክሲዩን ገበያ ሲያቋቁሙ ቁጠባን በማስተዋወቅና በማበረታታት ለግለሰቦች አንደ አማራጭ የፋይናንስ መንገድ ይፈጥራሉ ፡፡
ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ የሚያግዝ ከመሆኑም በላይ ለግሉ ዘርፍ የገንዘብ አቅርቦት ተደራሽነትን በማስፋት እና በኢኮኖሚ ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ መጋራት የካፒታል ገበያ መኖር ወሳኝ ይሆናል ፡፡
መደበኛ የአክሲዮን ገበያዎች በተለያዩ አገራት ለሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵውያን ወደ አገራቸው መምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው፣ ትርፋማ በሆነና ደኅንነቱ በተጠበቀ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩበትን ዕድል የሚፈጥርላቸው ተመራጭ አሠራር ነው ፡፡
በዚህ ደረጃውን የጠበቀ መድረክ መጠቀማቸው ኢንቨስትመንታቸው በቀላሉ ወደ ጥሬ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል ንብረት (ሊኩዲቲ) እንዲኖራቸው ከማስቻሉም በላይ፣ በጊዜ ሒደትም አግባብነት ያለው የዋጋ ትመና እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡
ዳያስፖራው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ አገራት ባንኮች ውስጥ በቁጠባ መልክ ቢያስቀምጥም፣ ይህ ነው የሚባል ወለድ እያገኘበት እንዳልሆነ የምናየው ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ትርፋማ ሊያደርግ የሚችል የኢንቨስትመንት ዕድል መፍጠር ከተቻለ ግን፣ ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተው በአገራቸው ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ የዳያስፖራ ባለሀብቶችን መሳብ ይቻላል፡፡
በእርግጥ እንዲህ አይነቱ የአክሲዮን ገበያ ከመፈጠሩ በፊት ጠንካራ ተቋማትን መገንባት የግድ ይላል ፡፡
በተለይም የሰለጠነ የሰው ሀይል በማብቃት ለአብነትም ኦዲተሮችን፣ የሂሳብ ባለሙያዎችን ፣የስቶክ ብሮከሮችን ፣የአክሲዮን ጠበቆችን ፣ የሚያሰልጥን ጠንካራ ተቋም ያስፈልገናል፡።
የፋይናንስ ገበያን ለመመስረት መሰረተ ልማት ላይ መዋለ ንዋይን በማፍሰስ ፣የፖሊሲ ለውጥ ማካሄድ የመሳሰሉ ስራዎችን መስራት የግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
እነዚህ ሁሉ የቤት ስራዎች ከተሰሩና የአክሲዩን ገበያን የሚከታተልና የሚቆጣጠር ህግ ከወጣ መድረኩን ማዘጋጀት አስቸጋሪ አይደለም ፡፡ በመሆኑም በዚህ ዙሪያ የንግዱ ህብረተሰብ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት ፡፡
በአጠቃላይ የካፒታል ገበያን ለመተግበር ኢትዮጵያ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ተቋማቷን አሠራር ማሻሻል ይገባታል ፡፡ ከሁለት እጅ በላይ የሚሆነው የኢትጵያ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ኢ-መደበኛ በመሆኑ ወደ መደበኛ ማምጣት፣ ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት፣ የኢንቨስትመንት ፖሊሲዎችን መቃኘት፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻል፣ የተረጋጋ ዋጋ እንዲኖር ማድረግ እና ለኢንቨስተሮች በቂ ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል ፡፡
በሀገሪቱ ያለው ንግድን ለማከናወን ያለው ከባቢ ሁኔታ (doing business environment) ስራዎች እየተሰራበት ቢሆንም አሁንም መሻሻል መቻል ይኖርበታል፡፡