የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤትና ሳክ ቢዝነስና ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት አብረው ለመስራት የሚስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስልጠናዎችን ለንግዱ ማህበረሰብ ማዳረስ ሲሆን ይህ የምክር ቤቱ አገልግሎት ኩባንያዎች ብቃት ባለው አመራር እንዲመሩና ዘላቂነት ያላቸው እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

የዚህ አንዱ አካል የሆነውና ምክር ቤቱ በቀጣይ ለሚተገብራቸው ስልጠናዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚስችለውን ስምምነት በስልጠናና ምርምር ዘርፍ ከአስራ አምስት አመት በላይ ልምድና ተሞክሮ ካለው ከሳክ ቢዝነስና ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት ጋር ተፈራርሟል፡፡

ይህ ስምምነት በተለይም ልምድና እውቀትን መሰረት ያደረጉ ስልጠናዎች ለንግዱ ማህበረሰብ እና ለስራ ፈጣሪዎች በማዳረስ የንግድ አመራር ክፍተቶችን ለመሙላት ትልቅ አጋጣሚ ነው በማለት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በስምምነቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

እንዲህ አይነት የትብብር መስኮች የምክር ቤቱን የስልጠና ተደራሽነት ከማስፋፋት ባለፈ ምክር ቤቱ በስራ ፈጠራ፤በፋይናንስ ተደራሽነት እንዲሁም በሌሎች አገልግሎቶች ዙርያ የሚያደርገውን ቀጣይ እንቅስቃሴዎች እንደሚያግዝ ዋና ጸሀፊው አክለው ተናግረዋል፡፡

ይህ ስምምነት በእውት ላይ የተመሰረተ የቢዝነስ አመራርን ተደራሽ በማድረግ ወጣቶች በስራ ፈጠራ የሚደርጉትን እንቅስቃሴ መደገፍ እንደሚያስችል የሳክ ቢዝነስና ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶ/ር አደራ አብደላ የመግባቢያ ሰነዱ በተፈረመበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረሰው ስምምነት በቅርቡ ተገባራዊ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ለየት ያለ የቢዝነስ አመረራ ስልጠናዎች እና መድረኮች የሚመቻቹበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን ከቻለ በቢዝነስ አመራር በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *