የአገሪቱ ባንኮች በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 2.3 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ሀብት አስመዘገቡ

ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱት ዘርፎች መካከል ግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የአገልግሎት ዘርፍ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ ዕድገት በማስመዝገብ ያለማቋረጥ በማደግ ላይ የሚገኘው ደግሞ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ የባንክ (የፋይናንስ) አገልግሎት ዘርፍ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያስመዘግብ የነበረውን ከፍተኛ ዕድገት፣ አገሪቱ በተለያዩ ቀውሶች በተናጠችበት የ2014 የሒሳብ ዓመትም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ማስቀጠል ችሏል። የአገሪቱ ባንኮች በ2014 የሒሳብ ዓመት ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ፣ የሰጡት ብድርና ሌሎች የሥራ አፈጻጸሞቻቸው ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ የታየበት ሲሆን፣ ከትርፍ አንፃርም የ2014 ሒሳብ ዓመት አፈጻጸማቸው ከቀደመው ዓመት የተሻለ መሆኑን ሪፖርተር የተመለከታቸው የየባንኮቹ ዓመታዊ ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡

ሁሉም የመንግሥትና የግል ባንኮች የትርፍ ምጣኔያቸው ይለያይ እንጂ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመትም በአትራፊነታቸው የቀጠሉ ሲሆን፣ የሀብት መጠናቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግም በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 2.3 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ሀብት ማስመዝገብ ችለዋል። ባንኮቹ ያስመዘገቡት አጠቃላይ

የሀብት መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም በ21 በመቶ ብልጫ እንዳለው መረጃዎቹ ያመለክታሉ።

ሁሉም ባንኮች የሰበሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 1.6 ትሪሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *