የኢትዮጵያ የውጭ እዳ የ5 በመቶ ቅናሽ አሳየ

አዲስ የተለቀቀ ብድር አገሪቱ ለእዳ ከከፈለችው ያነሰ መሆኑ አንደኛው ምክንያት ነው
በሳለፍነው ሳምንት የገንዘብ ሚኒስቴር የ2014 በጀት አመት የኢትዮጵያ ጥቅል እዳን አስመልክቶ ባወጣው ትንተና እንዳመላከተው የአገሪቱ የውጭ እዳ ከቀዳው አመት የ5 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
በዚህም በ2013 ከነበረው 29.5 ቢሊየን ዶላር ወደ 27.9 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም ከተለመደው አመታዊ እዳ ጭማሪ አንፃር ሲታይ አዲስ ክስተት ነው፡፡
ለውጭ እዳ በ1.6 ቢሊየን ዶላር መቀነስ አይነተኛ ምክንያት የተደረገው የአሜሪካ ዶላር ከሌሎች አገራት ገንዘብ አንጻር ጥንካሬ ማሳየቱ ሲሆን፡፡ በተጨማሪም በ2014 የተለቀቀው አዲስ ብድር አገሪቱ ለእዳ ከከፈለችው አንጻር ያነሰ በመሆኑ ነው፡፡
በ2014 አገሪቱ ለዋና እዳ ከከፈለችው አንፃር አዲስ የተለቀቀው ብድር የ552 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ ያለው ሆኖ ታይቷል፡፡
ሆኖም ወለድ እና ሌሎች ክፍያዎች ሲጨመሩበት ለእዳ የተከፈለው ገንዘብ መጠን ከተለቀቀ አዲስ ብድር አንጻር የግማሽ ያህል ብልጫ አለው፡፡
በበጀት አመቱ ወለድን ጨምሮ በጠቅላላው ለተወሰደ ብድር ኢትዮጵያ የከፈለችው 2.13 ቢሊየን ዶላር ሲሆን አዲስ የተለቀቀው መጠን ግን 1.08 ቢሊየን ዶላር ነው፡፡
አዲስ የተለቀቀ ብድር መጠን ሲቀንስ ይህ ለሁለተኛ አመት ነው፡፡ በ2012 ተለቆ ነበረ አዲስ ብድር 3.1 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን ይህ መጠን በ2013 ወደ 1.4 ቢሊየን ዶላር ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በ 2014 በጀት አመትም ቅናሽ ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡
የልማት ድርጅቶች ብድር ላለፉት ሶስት አመታት አለመውሰዳቸው ከቀም ሲል የተፈቀደላቸውም ብድር ፕሮጀክቶቻቸው እያለቁ በመሆኑ እና ተለቆ በመጠናቀቁ የአዲስ ብድር ፍሰት ለመቀነሱ እንደ አንድ ምክንያት የተነሳ ሲሆን፡፡ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር አገራት በተለይ የምእራብ አጋሮች ቃል የገቡትን ብድር ለመልቀቅ ዳተኛ መሆናቸውም ይታወሳል፡፡
በአመቱ ከተከፈለ እዳ 1.56 ቢሊየን ዶላር የሚሆነው በልማት ድርጅቶች የተከፈለ ሲሆን መእከላዊ መንግስ የከፈለው ደግሞ 567 ሚሊየን ዶላር ገደማ ነው፡፡
አዲስ ከተለቀቀው 1.08 ቢሊየን ዶላር ብድር ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ከአለም ባንክ የመጣ ሲሆን የማእከላዊ መንግስቱ ድርሻ 73 በመቶ ነበር፡፡ ቀሪው 27 በመቶ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኤርባስ አውሮፕላን ግዥ የተለቀቀ ብድር ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *