የወጪ ንግድን ለማሳደግ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ተጠየቀ

ብዙም እድገት የማያሳየውን የወጪ ንግድ ለማሳደግ የመንግስት ፖሊሲ ጣልቃገብነት ተጠየቀ፡፡የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ማክሰኞ የካቲት 1 ቀን 2014ዓ.ም በሒልተን ሆቴል ባካሔደው “የወጪ ንግድ እድሎች እና ፈተናዎች” በሚል ርእስ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ የተሳተፉ ላኪዎች የወጪ ንግድ ዘርፍ የተወሳሰቡ ችግሮች ያሉበት ዘርፍ በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የፋይናንስ አቅርቦት ፤ ዘመናዊ የግብይት ስርአት አለመኖር እና የውጪ ምንዛሬ እጥረት በውይይቱ የተነሱ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
አምራቹ ከውጭ በሚገቡ ግብአቶች ላይ መመርኮዙ እና ተተኪ የአገር ውስጥ ግብአቶች ላይ አለመሰራቱ ትልቅ ችግር እንደሆነ ተነግሯል፡፡ “ቡና ለመላክ ጆንያ ከውጭ የምናስገባው አሰራር ካልተለወጠ የትም መድረስ አይቻልም፡፡” ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዝደንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ መንግስት የንግድ ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጸው ም/ቤቱ ለፖሊሲ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦች ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡