የውጪ ባንኮች የሚገቡበት አሰራር የሀገር ውስጥ ባንኮችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባው ተገለጸ

የውጪ ባንኮች የሚገቡበት አሰራር የሀገር ውስጥ ባንኮችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባው ተገለጸ

የአዲስ አበባ ንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት የውጪ ባንኮች በሀገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲሰሩ መፈቀዱ ያለው እድልና ተግዳሮት በሚል ርእስ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነዉ ።

የም/ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መሠንበት ሸንቁጤ እንደተናገሩት ባለፉት በርካታ አስርት አመታት ኢትዮጵያ በሯን ለውጭ የፋይናንስ ተቋማት ዝግ አድርጋ ቆይታለች።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የፋይናንስ ዘርፉ በተለይም የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ መከፈቱ አይቀሬ እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ እየሆነ መጥቷል ፤ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ መቁረጡን የሚያመላክት እንደሆነም ያሳያል ሲሉ ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል ፡፡

ወ/ሮ መሠንበት አያይዘውም ‹‹የግል ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?፣ የሚኖረው የውድድር አውድ እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መንግሥት ይህንን ዕርምጃ ዕውን ማድረጉ ምን ጥቅም ያስገኛል? ምንስ ያሳጣል? የሚለው የአባሎቻችንም ሆነ የንግድ ምክርቤቱ ጥያቄ ይሆናል ብለዋል፡፡

የውጭ ባንኮች ወደ ሀገሪቱ መግባታቸው ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጥርጥር የለውም ያሉት ወ/ሮ መሠንበት አገባባቸው ግን የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል ፡፡

ይህም አጠቃላይ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ከማሳደግና ለአገር ከሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ የሚወሰድ ዕርምጃ ይሆናል ተብሎ እንደሚገመት ገልጸዋል ።

በሀገራችን ያሉ የንግድ ድርጅቶች እና ስራ ፈጣሪዎች በገንዘብ እጦት በሙሉ አቅማቸው ለመስራት ሲቸገሩ እንደሚስተዋል የገለፁት ወ/ሮ መሠንበት አዳዲስ ምርትና አገልግሎቶች ለማቅረብ እና ተወዳዳሪ ለመሆንም እንቅፋት ሆኗቸዋል ብለዋል፡፡

በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ምንጮች እና አይነቶች አለመኖር የብድር ፍላጎትን በበቂ ሁኔታ እንዳይሟላ አድርጓል የሚሉ ብዙ የም/ቤቱ አባላት አሉ ተብሏል ፡፡

የውጪ ባንኮች፣የኢኩዩቲ እና የሊዝ ፋይናንስ እንዲሁም የካፒታል/የአክሲዮን/ ገበያ የመሳሰሉት አለመኖራቸው የብድር ምንጮች እንዳይሰፉ አድርጓል ብሎ ንግድ ምክር ቤቱ እንደሚያምን ተገልጿል ፡፡

ከዚህ አንጻር የውጭ ባንኮች መግባታቸው በተለይ የንግዱን ማህበረሰብ ከመጥቀም አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳለ ተመላክቷል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *