የውጭ ምንዛሬ ክፍፍል ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ የብሄራዊ ባንክ ቦርድ ወሰነ።

የውጭ ምንዛሬ ክፍፍሉ ቀደም ሲል ከነበረው 70/30 ወደ 50/50 እንዲስተካከል አድርጓል።

50% ለብሄራዊ ባንክ 40%  የውጭ ምነዛሬውን ላመነጨው 10% ለባንኮች እንዲከፋፈል ተወስኗል::

እንደሚታወቀው በዚህ ጉዳይ አዲስ ቻምበር የቢዝነስ ማህበረሰቡን ለመደገፍ፣ በመንግስት የሚወጡ መመሪያዎች የታለመላቸውን ግብ እንዲያሳኩ በማድረግ ለሀገሪቱ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረከቱትን አስተዋፆኦ እንዲጎለብት ከማድረግ አኳያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተቀማጭ የውጪ ምንዛሬ አካውንት እና አጠቃቀም መመሪያ “The Retention and Utilization of Export Earnings and Inward Remittances Directives No. FXD/79/2022” እንዲሻሻል ሰፊ ስራዎችን ሰርቷል፡፡

ይህ የቀድሞ መመሪያ በአባላቶቹ የንግድ እንቅስቃሴና አብዛኞቹ በውጪ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ የተፈጠሩ ችግሮችን የበለጠ የሚያባብስ እንደሆነ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት አዲስ ቻምበር በተለያዩ ጊዜያት ባመቻቸው የውይይት መድረኮች ወቅት ሲያስረዱ ቆይተዋል፡፡

በተለይም መመሪያውን ተከትሎ በአምራች ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች ከውጪ ለሚያስመጧቸው መለዋወጫዎች፣ የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃዎች፣ የኬሚካል እና መሰል  ጥሬ ዕቃዎችን ለማግኘት እንዳላስቻላቸው አዲስ ቻምበር ለሚመለከታቸው በጥናት መልክ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በመሆኑም ከባንኮች ከሚያገኙት የውጪ ምንዛሬ 70% መቀነስ የማምረት ሥራቸውን ስለሚያስተጓጉል ምርታቸውን በተፈለገው መጠን እና ወቅት ለማምረት እንደሚቸገሩ፣  በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ ም/ቤታችን በመገንዘብ እንዲስተካከል የፖሊሲ አድቮኬሲ ስራ ሰርቷል፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመሪያ ከውጪ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተያይዞ በኢኮኖሚውና በግሉ ዘርፍ ላይ የተከሰቱ ችግሮችን የበለጠ እንዳያባብስ መመሪያው በድጋሚ እንዲታይ እና እንዲሻሻል ንግድ ምክር ቤቱ በጥናት ላይ የተመሰረተ የአድቮኬሲ ስራ ሲሰራ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን አሁን የተደረገው አዲሱ የውጪ ምንዛሬ ክፍፍል ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ እድገት ትልቅ እርምጃ እና አስተዋጽኦም ይኖረዋል፡፡

በዚህ ዙርያ ብዙ መሰራት የሚገባቸው ጉዳዮች የሚቀሩ ቢሆንም ይህንን የብሄራዊ ባንክ እርምጃ አዲስ ቻምበር በበጎ ጎኑ የሚመለከተው ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *