ጥራትን መሰረት አድርጎ መሥራት የምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው! - ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ

ዘንድሮ ለ9ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በታላቁ ቤተመንግሥት ተከናውኗል።
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ሽልማቱ ደረጃ ላይ ሳይንጠለጠል በጥራት መስፈርቶች ላይ መወሰኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
አክለውም እንደ ሀገር ለማደግ፣ የሕዝባችንን ኑሮ ለማሻሻል፣ ያለንን ራዕይ ለማሳካት ዛሬ ባለንበት ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ካልሆንን፤ የመወዳደር አቅማችንን ካላጎለበትን፣ ምርቶቻችንን በዓይነትና በጥራት ለማቅረብ፣ በዓለም ገበያ ውስጥ ለመግባት ካልቻልን፣ በዚህ ሂደት ጥራት ማዕከላዊ ቦታ ይዞ ካልተገኘ ዕድገታችን ውሱን ይሆናል፤ ባለንበት እንድንዳክር ያደርገናል ብለዋል።
ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የሀገራችንን ራዕይ እውን ለማድረግ ጥራትን መሰረት አድርጎ መሥራት የምርጫ ብቻ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ ጥራት ያለው ምርት ለማምረትና አገልግሎት ለመስጠት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ሲሉ አሳስበዋል።
የጥራት ሽልማት ባልተለመደበት ሁኔታ ይህንን ተሞክሮ ይዘው በመምጣታቸው የጥራት ሽልማቱን ያዘጋጁ አካላትን አመስግነዋል።
በሽልማት መርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ አድናቆት የተቸራቸው ሦስተኛና ሁለተኛ ደረጃ የጥራት ተሸላሚዎች ቢኖሩም አንደኛ ደረጃ ሽልማቱ ሳይሰጥ ተመልሷል።
ይህም የሆነው የጥራት ደረጃው የሚጠይቀውን መስፈርት ሊያሟላ የቻለ ተቋም ባለመገኘቱ ነው ተብሏል።