የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከዛምቢያ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

መጋቢት 20 2009 ዓ.ም በዛምቢያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዛምቢያው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ቻግዋ ሉንጋ ጋር መክረዋል ሲል ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ዘግቧል ። በዚህም የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ዛምቢያ ቁርጠኛ መሆኗን ፕሬዚዳንት ሉንጉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አረጋግጠውላቸዋል ብሏል። የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና የዛምቢያ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ደግሞ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። የዛምቢያ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አንድሪው ሲንያንግዌ  የመግባቢያ ሰነዱ መፈረም የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት እንደሚያሳድግ ተናግረዋል ሲል ዘገባው አመልክቷል።

ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ በተለያዩ ዘርፎች ትብብራቸውን ማጠናከር የሚያስችሏቸውን ስምምነቶች መፈራረማቸውን የዘገበው ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ፤ ሁለቱ ሀገራት በኮሙዩኒኬሽን እና በውሃ አስተዳደር ዘርፍ ሁለት ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ገልጿል። ከስምምነቱ ፊርማ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ የነበራቸው የዛምቢያ የኢንፎርሜሽን እና ብሮድካስት አገልገሎት ሚኒስትር ሙለንጋ ካምፓምባ፥ ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ በኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ያደረጉት ስምምነት ሀገራቱ በሚዲያው ኢንዱስትሪ ተባብሮ መስራት ያስችላቸዋል ብለዋል።

በ28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በአዲስ አበባ ቆይታ የነበራቸው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት፥ ሃገራቸው ከኢትዮጵያ የግብርና፣ የቆዳና የጨርቃጨርቅ የልማት ስኬቶች ልምድ መውሰድ እንደምትፈልግ መናገራቸውን ፋና በዘገባው አስታውሷል።ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪን በማስፋፋት ረገድ እያሳየች ያለውን ዕድገት በተሞክሮነት መውሰድ እንፈልጋለን ሲሉም ገልፀው ነበር ብሏል።