የፋርማሲ የንግድ ትስስር ክለብ አባላት ምክክር አደረጉ

የጉምሩክ አሰራር በታሪፍ አወሳሰንና ስራዎች ከመጓተት ጋር ያሉ ችግሮች፣ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ የሚያቀርቡበት ሂደትና አሰራር፣ መንግስት በፖሊሲና በማበረታቻነት ያስቀመጣቸውን ወደ በስራ ላይ ከማዋል ረገድ ያሉ ችግሮች የፋርማሴውቲካል ዘርፍን አንቀው ከያዙት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ በፋርማሲና ተያያዥነት ባላቸው የስራ መስኮች የተሰማሩ የግልና የህዝብ ተቋማት የተካፈሉበት 3ኛ የምክክር መድረክ ታህሳስ 6፣ 2009 ዓ.ም. በኢሊሊ ሆቴል ተካሄደ፡፡

የእለቱ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተዘጋጀ ሲሆን የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ ያየህይራድ አባተ ስነ ስርዓቱን በመክፈቻ ንግግር ከፍተው በመጨረሻም የማጠቃለያ መልእክትና በቀጣይ ምን እንደሚከተል ጠቁመዋል፡፡

የፋርማሲውቲካል ዘርፍ በዓለም ደረጃ የ1.3 ትሪሊየን ዶላር ገበያ እንዳለውና ይህም በየዓመቱ ከ 3 ‐ 6% እድገት እንደሚያሳይ አወያዩ ጠቅሰው፤ አፍሪካ በበኩሉ የ30 ቢሊዮን ዶላር ገበያና በየዓመቱ የ10% እድገት እንዲሁም በኢትዮጵያ ደግሞ የ800 ሚሊዮን ዶላር ገበያና 25% ዓመታዊ እድገት እንደሚታይበት ጠቁመዋል፡፡ ይህም ትልቅ ገበያ ለባለሃብቶች ሰፊ እድል እንደሆነ ተሰምሮበታል፡፡

ዘርፉ በፖሊሲ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ቢሆንም ጉምሩክ አካባቢ ባለው የተጓተተ ሂደት፣ ለዘርፉ መለዋወጫዎች የተቀመጠው የታሪፍ መጠን ትግበራ ላይ ችግር የታየበት መሆኑ እንዲሁም የባንክ አገልግሎትን በተመለከተ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ የሚታየው ክፍተት አጽእኖት የተሰጣቸው የዘርፉ አንገብጋቢ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *